አስተርጓሚ የማግኘት መብት ያለው ማነው?
የሚነገረው ካልገባዎት እና የሚፈልጉትን መናገር ካልቻሉ በመረጡት ቋንቋ አስተርጓሚ የማግኘት መብት አለዎት። እለት ተለት ኖርዌጂያን ቢናገሩም አስተርጓሚ የማግኘት መብት ሊኖርዎት ይችላል።
አስተርጓሚ ማን ያዛል?
ብቃት ያለው አስተርጓሚ የማዘዝ ኃላፊነት ያለበት የጤና አገልግሎት ሰጪው ነው።
አስተርጓሚ ያስፈልግ እንደሆነ ለማወቅ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። በዋነኛነት አስተርጓሚ አስፈላጊ እንደሆነ የሚገመግሙት የጤና ባለሙያዎች ናቸው። እንዲሁም እርሶ አስተርጓሚ ያስፈልጋል ብለው ካሰቡ ማሳወቅ ይችላሉ፣ ለምሳሌ ቀጠሮ ሲያሲዙ። እንዲሁም ወደ ጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋም በመደወል በቋንቋዎ አስተርጓሚ እንዲይዙሎት መጠየቅ ይችላሉ።
የስክሪን ወይም የስልክ አስተርጓሚዎች በክፍሉ ውስጥ ከሚገኝ አስተርጓሚ አንዳንድ ጊዜ ጥሩ አማራጭ ሊሆን ይችላል። ።
የመንግስት አካላት ብቁ አስተርጓሚዎችን የመጠቀም ግዴታ እንዳለባቸው የሚገልጸው የተርጓሚዎች ሕግ ነው።
ማን ሊያተረጉም ይችላል?
አስተርጓሚው የአስተርጓሚነት ትምህርት ወይም ስልጠና የወሰደ ሰው መሆን አለበት።
ልጆችን እንደ አስተርጓሚ መጠቀም የለበትም። ሌሎች ዘመዶች ወይም ሰዎች የአስተርጓሚነት ትምህርት ካልወሰዱ ከብቁ አስተርጓሚ ይልቅ ጥቅም ላይ መዋል የለባቸውም።
አስተርጓሚ ሲጠቀሙ ምን ማድረግ አለብዎት?
የትኛውን ቋንቋ እንደሚመርጡ በትክክል ለጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋሙ መንገር አስፈላጊ ነው።
አስተርጓሚ ለምክክር ቀጠሮ ከታዘዘ በቀጠሮው ሰዓት መገኘት በጣም አስፈላጊ ነው። ቀጠሮው በተያዘበት ሰአት መገኘት ካልቻሉ ቢያንስ ከ24 ሰአት በፊት መሰረዝ አለቦት። ይህን ካላደረጉ ለምክክር ቀጠሮው መክፈል አለቦት። በተለይ አስተርጓሚ ሲታዘዝ ይህንን ማስታወስ ጠቃሚ ነው።
አስተርጓሚ ምንድን ነው እና የአስተርጓሚው ተግባራት ምንድን ናቸው፧
አስተርጓሚው ሚስጥርን የመጠበቅ ግዴታ አለበት። በትርጉም ሰአት በንግግር ውስጥ የሚሰማውን ማንኛ ውንም ነገር ለማንም መናገር አይችልም።
አስተርጓሚው የተነገረውን ብቻ መተርጎም አለበት፣ ምክር መስጠት ወይም የራሱን አስተያየት መጨመር የለበትም። አስተርጓሚው ገለልተኛ መሆን እና ከማንም ጋር መወገን የለበትም።
እንደ ታካሚ ንግግሩን የሚያደርጉት ከጤና አገልግሎት ሰጪው ጋር ነው። ስለዚህ ሁሉም ጥያቄዎች ወደ አስተርጓሚው ሳይሆን ለጤና ባለሙያው መቅረብ አለባቸው።
ለአስተርጓሚው የሚከፍለው ማነው?
በጤና አገልግሎት ተቋም ውስጥ እንደ ታካሚ አስተርጓሚ ለእርስዎ ነፃ ነው። ይህ ተግባራዊ የማይሆነው ወደ ጥርስ ሀኪምቤት የሚሄዱ ከሆነ እና ለጥርስ ህክምናው እራስዎ መክፈል ካለቦት ነው። ይህ ሲሆን ለአስተርጓሚውም እርሶ መክፈል አለቦት።
ቅሬታ ማቅረብ ይችላሉ
እርሶ አስተርጓሚ ያስፈልግኛል ብለው ቢያስቡም አስተርጓሚ ካላገኙ ታካሚ ወደሆኑበት ተቋም ቅሬታዎን ማቅረብ ይችላሉ። እንዲሁም በሚኖሩበት ክልል ውስጥ ላለው የመንግስት አስተዳዳሪ፣ የታካሚ እና የተጠቃሚ መብት ጠባቂ (በኖርዌይኛ) ወይም የእኩልነት እና የመገለል መብት ጠባቂ (በኖርዌይኛ) ቅሬታዎን ማቅረብ ይችላሉ።
በአስተርጓሚው ደስተኛ ካልሆኑ፣ ስለዚህ ጉዳይ ታካሚ ወደሆኑበት ተቋም ቅሬታዎን ማቅረብ ይችላሉ።